በሶላር ኢነርጂ ሙያ ከተለያዩ ክልሎች ለመጡ ሰልጣኞች የተሰጠ ስልጠና ማጠናቀቂያ…!!!

የኢትዮጵያ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውሃና ተያያዥ ዘርፎች በሀገሪቱ ፈጣን ልማት ለማምጣት የሚያስችል የሰው ሃይል አቅምን መገንባት፣በዘርፉ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማምጣት፤ በክልሎች የሚገኙ የውሃ ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት ሂደት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ የቴክኒካል ድጋፍና የብቃት ምዘና አገልግሎት መስጠት እና የዘርፉን የማስፈፀም አቅም ለማሳደግ የስፔሻላይዝድ ላቦራቶሪ አገልግሎት ማከናወንን መሰረት አድርጎ እንዲሰራ በመንግስት የተቋቋመ ኢንስቲትዩት ነው፡፡

ኢንስቲትዩቱ ራሱን በሰው ሀይልና በማቴሪያል አደራጅቶ ወደ ስራ ከገባ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በ20 መደበኛ የስልጠና ዘርፎች ከተለያዩ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ ከ3200 በላይ ለሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች፤አሰልጣኞችና ሰልጣኞች አጫጭር ተግባር ተኮር ሥልጠናዎችን የሰጠ ሲሆን፤ እስከ 2012 ዓ.ም በጀት ዓመት መጨረሻም የሰልጣኞቹን ቁጥር 4500 ለማድረስ እየሰራ ይገኛል፡፡

የ2012 ዓ.ም ዕቅድ አንድ አካል የሆነው ለ18 ቀናት የቆየ በቲዎሪና በተግባር የተደገፈ በSolar Water Pumping System installation, Operation and Maintenance ሥልጠና ከትግራይ፤ ከአፋር፤ ከአማራ፤ ከኦሮሚያ፤ ከቤኒሻንጉል፤ ከጋምቤላ፤ ከሐረሪ ክልሎችና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ከአዋሽ ተፋሰስ ባለሥልጣን ውሃ ቢሮዎች፤የከተማ ውሃ አገልግሎት እና መስኖ ልማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ተሰጥቷቸዋል፡፡

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ የተገኙት አቶ ታመነ ሀይሉ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ባስተላለፉት መልዕክት በተለይ 13 ወራት ፀሀያማ ተብላ ለምትጠራው ኢትዮጵያ በSolar Water Pumping System installation, Operation and Maintenance ሥልጠና መስጠቱ እንደ ሀገር ያሉብንን የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የሀይል አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል፡፡ በሶላር ኢነርጂ ላይ ሥልጠናዎችን በሰፊው ለመስጠትም ኢንስቲትዩቱ ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና አድራ-ኢትዮጵያ ከተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር የሙያ ደረጃዎች፤የስርዓተ-ትምህርት ቀረፃና የመመዘኛ መሳሪያዎች ዝግጅት ስራ ተጠናቋል፡፡ በቀጣይ በስርዓተ-ትምህርቱ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ 2200 ለሚሆኑ በሶላር ኢነርጂ ሙያ በመካከለኛ ደረጃ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን በአጭር ጊዜ ከየካቲት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ በማሰልጠን ወደ ስራ ለማሰማራት መታቀዱን አቶ ታመነ ጠቅሰዋል፡፡

ከሰርተፊኬት አሰጣጡ በኋላ የሰልጣኞች ተወካይ ሰልጣኞቹን በመወከል ሀሳባቸውን የሰጡ ሲሆን የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተለይ የሶላር ኢነርጂን በመጠቀም የማህበረሰባቸውን የንፁህ መጠጥና ውሃና ሳኒቴሽን፤ የሀይልና የመስኖ ችግሮችን ሊቀርፉ የሚችሉ በተግባር የተደገፉ ሥልጠናዎችን መስጠቱ ለሌሎችም የፌዴራል ተቋማት አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በሥልጠና ቆይታቸውም አሰልጣኞቹ፤ የኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ሰራተኞች ሲያደርጉላቸው ለነበረው ድጋፍ ምስጋናቸውንምን አቅርበዋል፡፡

ታህሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት
የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት