በሶላር ኢነርጂ ሙያ የሥልጠና ማቴሪያሎች ዝግጅት ቫሊዴሽን ወርክሾፕ…!!!

የኢትዮጵያ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሶላር ኢነርጂ ሙያ በመካከለኛ ደረጃ ባለሙያዎችን ለማፍራት ሥልጠና በሰፊው ለመስጠት ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ እና ከፍተኛ የፋይናንስና ቴክኒካል ድጋፍ እያደረገ ከሚገኘው የአድቬንቲስት የልማትና ተራድኦ ድርጅት (ADRA-Ethiopia) ጋር በመተባበር በሶላር ሙያ ከደረጃ II-IV አዲስ በተዘጋጁ የስርዓተ-ትምህርት ሰነዶች ዙሪያ የቫሊዴሽን ወርክሾፕ ከኦሮሚያ፤ከትግራይ፤ከአማራ ክልሎች እንዲሁም ከፌዴራል ተቋማት ከተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከፍተኛ አመራሮች ጋር ምክክር ተደርጓል፡፡

መድረኩን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ ኃይሉ ሲሆኑ፣ በሶላር ኢነርጂ ሙያ ከየካቲት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ በፓይለት ደረጃ በትግራይና አማራ ክልሎች በተመረጡ 4 ኮሌጆች ከ2200 ያላነሱ ወጣቶችን በአጫጭር ሥልጠና በማሰልጠን ወደ ስራ ለማሰማራት የሚረዳ የስርዓተ-ትምህርት ዝግጅት፤ የማሰልጠኛ እና የመማሪያ ሰነዶች /TTLM/ እና የምዘና መሳሪያዎች ዝግጅት በ ‘ADRA-Ethiopia’ የቴክኒካልና ፋይናንሻል ድጋፍ መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡ የቫሊዴሽን ወርክሾፑ ዋነኛ ዓላማም የተዘጋጁትን የማሰልጠኛ ሰነዶች ለሚመለከታቸው የዘርፉ የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች በማቅረብ ተጨማሪ ግብአቶችን ለማሰባሰብ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስቴር ዴኤታ በመክፈቻ ንግግራቸው የተፈጥሮ ሃብት በመኖሩ ብቻ የልማትና የእድገት ዋስትና ሊረጋገጥ እነደማይችል፤ ዘላቂ የልማት ውጤት ሊኖር የሚችለው በሰው ኃይል ግንባታ፣ በምርምር እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ከተደገፈ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተለያዩ አካላት የጋራ ጥምረት የተዘጋጀው የሶላር ኢነርጂ የሙያ ደረጃ ተጠናቆ ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ሲገባ ከሶላር ኤሌክትሪፊኬሽን ባሻገር በንፁህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፤ በመስኖ ልማትና በሃይል ዘርፍ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በመፍታት ሀገራቸውንና ራሳቸውን መጥቀም የሚችሉ ወጣትና ብቁ ባለሙያዎችን በስፋት ለማፍራት ያግዛል ብለዋል፡፡

ለቫሊዴሽን መድረኩ ውይይትና ግብአት ለመስጠት የሚያመቹ መነሻ ሁለት ፅሁፎች ማለትም የሶላር ኤሌክትሪፊኬሽን ሙያ ደረጃ ለአጫጭር ስልጠናዎች ያላቸው ፋይዳዎች እና የሶላር ፒቪ ስርዓተ-ትምህርት መሳሪያዎች ዝግጅትና ቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት በአቶ ፍፁም ጥላሁን ከፌ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ ኤጀንሲ ቀርቧል፡፡

የውይይት መድረኩ 3ኛው የመወያያ ሰነድ ርዕስ በሶላር ኢነርጂ ሙያ ደረጃዎች፤ ስርዓተ-ትምህርትና TTLM/ የምዘና መሳሪያዎች ዝግጅት ላይ የአድራ-ኢትዮጵያ ሚናዎችና ቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት ሲሆን ፅሁፉ ከአድራ-ኢትዮጵያ በአቶ ብስራት አበራ የቀረበ ሲሆን የተከናወኑና ቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት በሰፊው ለታዳሚዎች ቀርቧል፡፡ አቶ ብሥራት በፅሁፋቸው ማጠቃለያ ADRA-Ethiopia በሀገር ደረጃ የማህብረሰቡን ችግሮች ሊፈቱ በሚችሉ በርካታ ፕሮጀክቶች የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በቀጣይም በሶላር ኢነርጂ ሙያ 2200 ለሚሆኑ ለተመረጡ 2 የግል እንዲሁም 2 የመንግስት ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች ላይ ሥልጠና ለመስጠት በሚያስችል ቁመና ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በቀረቡት ሰነዶች ላይ የመድረኩ ተሳታፊዎች ያላቸውን ሙያዊ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ ሀይሉ፤ የፌ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ክብረት እና (ADRA-Ethiopia) አቶ ብስራት አበራ ምላሾችና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡

ክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ውሃ፤መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ምላሽና የማጠቃለያ ሀሳብና አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና የፌ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ ኤጀንሲ አመራሮች አብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረሙ በኋላ የቫሊዴሽን ወርክሾፑ ፍፃሜ ሆኗል፡፡

ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት
የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት