የካይዘንና የስራ ፈጠራ ክህሎት (ኢንተርፕሪነርሺፕ) ሥልጠና በአዳማ ከተማ …!

የኢትዮጵያ ዉሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከመንግሥት በተሰጠው ስልጣንና ተግባራት መሰረት ለኢንስቲትዩቱ እና ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና አሰልጣኞች ተከታታይነት ያላቸውና በዘርፉ ስልጠናዎች ላይ ፋይዳቸው የጎላ የሥልጠና፤የማስተማሪያና መማሪያ ማቴሪያሎች ዝግጅት የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

በዚሁ መሰረት የካይዘንና የስራ ፈጠራ ክህሎት (ኢንተርፕሪነርሺፕ) ሥልጠና በክልሎች የሚገኙ 9 ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች የሚገኙ አሰልጣኞችን በካይዘንና የሥራ ፈጠራ ክህሎት አቅማቸውን በመገንባት በአካባቢያቸው የሚገኙ በውኃ ሙያ የተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን እንዲደግፉ ለማስቻል የሚረዳ ሥልጠና በአዳማ ከተማ በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራም ድጋፍ እና የብቃት ምዘና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ወቅት የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ፍቃዱ እንደተናገሩት ስልጠናው በዋነኝነት ሁለት ፋይዳዎችን መሰረት አድርጎ የሚሰጥ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ሥልጠና፡-

1. በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች የሚገኙ የውሃ አቅርቦት፤የመስኖ እና ኤሌክትሮመካኒካል አሰልጣኞች የኢንተርፕሪነርሺፕ ክህሎት እንዲኖራቸው ማድረግ ሲሆን፤ በተያያዘም
2. ከሥልጠናው በኋላ አሰልጣኞቹ የአካባቢያቸውን የልማት ቀጠና እና በውሃ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን በካይዘን አተገባበርና በሥራ ፈጠራ በመደገፍ ስራ ፈላጊ የሕብረተሰብ ክፍሎች ስራ እንዲፈጥሩ ለማስቻል ይረዳል፤ ብለዋል፡፡

ከሥልጠናው የሚጠበቅ ውጤትን በተመለከተ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ሲገልፁ ከስልጠናው ፡-

 በካይዘንና የስራ ፈጠራ ክህሎት አቅማቸው የተገነባ አሰልጣኞች፤
 ሁሉም ሰልጣኞች በስልጠናው ማጠናቀቂያ ወደ ኮሌጃቸው ሲመለሱ የሚተገብሯቸው የድርጊት መርሃ-ግብሮችን እንዲያዘጋጁ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራም ድጋፍ እና የብቃት ምዘና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የውሃውን ዘርፍ አቅም ግንባታና ቴክኖሎጂ ሽግግር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በውሃ ዘርፎች ላይ ሥልጠና እየሰጡ ለሚገኙ በክልሎች ለሚገኙ ኮሌጆች የቴክኒካል ድጋፍ በፖሊቴክኒክ ኮሌጆቹ ለሚገኙ አሰልጣኞችና ሀላፊዎችን አቅም ለማሳደግ ካለፉት ጊዜያት በበለጠ መልኩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት (17-6-12)